የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ (ኢ.ም.ቋ.) አጭር ታሪክ

ጳውሎስ ካሡ (ዶ/ር)

ከመስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤቶች መከፈት ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ መስማት የተሳናቸው ማኅበረሰብና የምልክት ቋንቋ እንደ ነበረ የሚጠቁሙ በጽሑፍ ያልሠፈሩ የተወሰኑ መረጃዎች አሉ፡፡ በ1950ዎቹ አጋማሽ ላይ ከሰሜን አሜሪካና ስዊድን የሙጡ ሚሲዮናዊያን በአዲስ አበባና በከረን (በቀድሞዋ የኢትዮጵያ ግዛት ኤርትራ) የመጀመሪያዎቹን የመስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤቶች ከፈቱ፡፡ በ1956 ዓ.ም ትምህርት ቤታቸውን በአዲስ አበባ የከፈቱት አሜሪካውያን በማስተማሪያነት የተጠቀሙት ቋንቋ በወቅቱ በጥሩ የዕድገት ደረጃ ላይ የነበረውን የአሜሪካን የምልክት ቋንቋ ሲሆን፣ በከረን ውስጥ ትምህርት የጀመሩት ስዊድናውያን ደግሞ የኖርዲክ ሀገራት የሚጠቀሙበትን አሁን የስውዲን የምልክት ቋንቋ በመባል የሚታወቀውን ነበር፡፡ በሁለቱ የምልክት ቋንቋዎች መካከል ልዩነት ቢኖርም፣ በኢትዮጵያውያን ተማሪዎቻቸው ሁለቱም እኩል ተቀባይነት አግኝተው የአሜሪካኑ በመሐል ሀገር፣ የስውዲኑ በሰሜን ኢትዮጵያ በሥፋት ጥቅም ላይ ውለው እንደ ነበረ የወቅቱ ተማሪዎች ይናገራሉ፡፡ በምልክት ቋንቋ በመማር የመጀመሪያዎቹ የነበሩት እነዚህ ተማሪዎች ሐሳባቸውን ለመግለጽ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ዐውቀውም ሆነ ሳያውቁ በአሜሪካና በስውዲን ምልክት ቋንቋዎች ውሥጥ አቻ ለሌላቸው ቃላት የቤት ውስጥ ምልክት ቋንቋ ምልክቶችን እንዲሁም አዳዲስ ሀገር በቀል ምልክቶችን በማስተዋወቅና በሁለቱም የምልክት ቋንቋዎች ውሥጥ ያሉ ምልክቶችን ሀገራዊ ይዘት እንዲኖራቸው አድርገው በመለወጥ ሀገራዊ ሐሳቦችን ለማስተላለፍ በመጠቀም ዛሬ የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ በመባል ለሚታወቀው ቋንቋ መሠረት ጥለዋል፡፡ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሁለቱ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በሥራና በተለያዩ ምክንያቶች መገናኘት ሲጀምሩ፣ የአሜሪካም የስዊድንም የምልክት ቋንቋ ያልሆነ ከላይ የተጠቀሱት ሀገራዊ ምልክቶች ተፅዕኖ ያለበት አዲስ የምልክት ቋንቋ ብቅ ማለት ጀመረ፡፡ በሚሲዮናዊያኑ ትምህርት ቤቶች በመማርና የአሜሪካና የኖርዲክ ምልክት ቋንቋዎችን በመጠቀም ስለ ምልክት ቋንቋ ግንዛቤ ያዳበሩት መስማት የተሳናቸው ኢትዮጵያውያን፣ ይህንን ጅምር ሥርዓት ለማስያዝ ሙከራ ማድረግ ጀመሩ፡፡ የቤት ውስጥ ምልክት ቋንቋዎችም ሆኑ ከላይ የተገለጹት ጅምሮች የራሳቸው የጣት ፊደላት ስላልነበራቸው ሙከራው ያነጣጠረው የግእዝ ፊደላት አቻ የሆኑ የጣት ፊደላት በመፍጠር ላይ ነበር፡፡ አንዳንድ መጣጥፎች ይህንን ወቅት ኢምቋ የተጀመረበት ወቅት አድርገው ለማቅረብ ይሞከራሉ (ይኄይስ፣ 2003)፡፡ ይህ ወቅት የኢምቋ የጣት ፊደላት የተጀመሩበት እንጂ ኢምቋ የተጀመረበት ወቅት አይደለም፡፡

     በ1964 ዓ.ም አቶ ምናሴ አበራ የተባሉ መስማት የተሳናቸው ግለሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ የግእዝ ፊደላት አቻ የሆኑ የጣት ፊደላትን የመፍጠር ሙከራ አድርገው፣ በወቅቱ አጠራር  የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ለነበሩት መስማት የተሳናቸው ጓደኛቸው ለአቶ ተክለሃይማኖት ደርሶ ያሳያሉ፡፡ ሁለቱ ጓደኛሞች ፈጠራውን በጋራ ካጠኑትና አንዳንድ መሻሻሎችን ካደረጉበት በኋላ የወቅቱ የመስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ሊቀመንበር ለነበሩት ሌላ መስማት የተሳነው አቶ ኃይሉ የሱነህ የተባሉ ግለሰብ አቀረቡ፡፡ አቶ ኃይሉ ለጉዳዩ ትኩረት በመሥጠት ሙከራውን የሚያጠና ሦስት ዓባላትን ያቀፈ የኮሚቴው ዓባላትም እራሳቸው አቶ ምናሴ፣ አቶ ተክለሃይማኖት እና አቶ ኃይሉ ነበሩ፡፡ የአቶ ምናሴ ፈጠራ ትኩረት፣ የግእዝ ፊደላትን ቅርጽ በአምስቱ ጣቶች በመሥራት ላይ (ለምሳሌ፡- ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መ፣ ሠ፣ ረ፣ ቀ፣ በ፣ ተ፣ ቸ፣ ኀ፣ ነ፣ ወ፣ ዐ፣ ዘ፣ የ፣ ደ፣ ጀ፣ ጠ፣  ፈ፣ ጰ፣ ፐ)፣ ቅርፃቸውን በአምስቱ ጣቶች መሥራት አስቸጋሪ ለሆኑት ፊደላት ደግሞ ከአሜሪካ የምልክት ቋንቋ የጣት ፊደላት በመዋስ፣ (ለምሳሌ ረ፣ ነ፣ አ፣ ጸ)፣ ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን መጠቀም አስቸጋሪ በሆኑባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ደግሞ በዘፈቀደ በመፍጠር (ለምሳሌ ሸ፣ ኘ፣ ኸ፣ ዠ፣ ገ፣ ጨ፣ ፀ) ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አቶ ምናሴ ለካዕብ፣ ሣልስ፣ ራብዕ፣ ኀምስ፣ ሳድስ እና ሳብእ የፊደል ቁልፎች (አናባቢዎች) አዘጋጅተው ነበር፡፡ “የአንዳንዶቹ ቁልፎች መሠረታዊ ምልክት እስከ 180 ዲግሪ ድረስ ማዞር ያስፈልግ ስለ ነበረ እኔና አቶ ምናሴ ተነጋግረን በአሁኑ ጊዜ ያላቸውን መልክ እንዲይዙ አድርገናል፡፡ … የግዕዙን ድምፅ የሚወክሉት ላይም በመጀመሪያ አቶ ምናሴ ያዘጋጃቸውን አንዳንዶቹን ለውጠናል፡፡” (ቃለ መጠይቅ፣ ተክለሃይማኖት፣ 2004)፡፡

     የአቶ ኃይሉ ኮሚቴ ፈጠራውን ካጠና በኋላ ውጤቱን ለሙከራ አቀረበ፡፡ ሙከራው አጥጋቢ ሆኖ ስለ ተገኘ መስማት የተሳናቸውን ለማስተማር ጥቅም ላይ እንዲውል በማኅበሩ በኩል ለትምህርት ሚኒሥቴር ተላለፈ፡፡ ትምህርት ሚኒሥቴርም መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤቶች አስተያየት እንዲሠጡበት አድርጎ፣ የኀምሃ ደስታ የመስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት ለ “ወ” ተሰጥቶ በነበረው ምልክት ላይ ብቻ ማሻሻያ አቅርቦ ተቀባይነት ስለ አገኘ አሁን ጥቅም ላይ ያለው ምልክት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ኮሚቴው ማሻሻያውን የተቀበለው የ “ወ” ምልክት ጉድለት ኖሮበት ሳይሆን፣ አብሮ የመሥራት ፍላጎትና ስሜት እንዲዳብር በማለት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ፈጠራው የትምህርት ሚኒሥቴርን ተቀባይነት እና ድጋፍ ስላገኘ፣ መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች በሚገኙባቸው ትምህርት ቤቶች በሙሉ ጥቅም ላይ እንዲውል በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ የትምህርት ቤቶች  ጽሕፈት ቤቶች ሰርኩላር ተላለፈ፡፡ አቶ ምናሴ የኢምቋ የጣት ፊደላት የፈጠራ የቅጂ መብት ያልተሰጣቸው ለምን እንደሆነ አቶ ተክለሃይማኖት (2004) እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡ “በወቅቱ አንስቼ የተነጋገርንበት ጉዳይ ነበር፡፡ አቶ ምናሴ ደግና ሩቅ አሳቢ፣ ለወገኖቹ ተቆርቋሪ በመሆኑ፣ ያስብ የነበረው ፈጠራው ለመስማት የተሳናቸው የሚሠጠውን ጥቅም እንጂ የግል ጥቅሙን አልነበረም፡፡ የፈጠራ ቅጂ ለእርሱ ምንም እንዳልነበረ  ነበር የነገረኝ፡፡”

የጣት ፊደላቱ ፈጠራ በባዕድ የምልክት ቋንቋ በመማራቸው ባሕላቸውን ለመረዳትና ከማኅበረሰቡ ጋር ለመግባባት ችግር የነበረባቸውን ተማሪዎች ችግር ከመፍታቱም በላይ ብሔራዊ የምልክት ቋንቋ መዝገበ-ምልክት ለማዘጋጀት መሠረት ጥሏል፡፡

  

   የጣት ምልክቶቹ በትምህርት ሚኒሥቴር ተቀባይነት ካገኙ  በኋላ የምልክት ቋንቋ መዝገበ-ምልክት ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ማኅበሩ ስለመነበት፣ መዝገበ ምልክት ለማዘጋጀ ጥረት ማድረግ ጀመረ፡፡ በዝግጅቱ ላይ የመስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤቶች እንዲሳተፉ ለማድረግ የግድ ወደ  ትምህርት ሚኒሥቴር መሄድ ያስፈልግ ነበር፡፡ በወቅቱ ለዕድገት በኅብረት ዘመቻ፣ አቶ ምናሴ ወደ ደብረብርሃን አቶ ተክለሃይማኖት ደግሞ ወደ አሰላ ዘምተው ስለነበረ፣ ጉዳዩን የመከታተል ኃላፊነት የወደቀው በአቶ ኃይሉ ትከሻ ላይ ነበር (ተክለሃይማኖት፣ 2004)፡፡ በአቶ ኃይሉ ጥረትም በ1968 ዓ.ም በትምህርት ሚኒሥቴር ሰብሳቢነት በተደረገ፣ የሁለቱ የመስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤቶች (መካኒሳ እና አልፋ)፣ የመስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር፣ የትምህርት ሚኒሥቴር የልዩ ትምህርት ክፍል ተወካዮች በተገኙበት ስብሰባ ላይ የእነዚህን አራት አካላት ተወካዮችን ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ “የአማርኛ” መዝገበ ምልክት እንዲያዘጋጅ ተወሰነ፡፡ በዚሁ መሠረትም ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፣ ከአባላቱም ሁለቱ አቶ ተክለሃይማኖት ደርሶና አቶ ኃይሉ የሱነህ ነበሩ፡፡ ኮሚቴው ሲቋቋም አቶ ተክለሃይማኖት ከአሰላ ወደ አዲስ አበባ የዘመቻ መምሪያ ተመልሰው ስለ ነበረ፣ የኮሚቴው አባል የመሆን ዕድል ሲያገኙ፣ አቶ ምናሴ ግን እሩቅ ስለነበሩ፣ ኮሚቴው ውስጥ አልገቡም፡፡ ኮሚቴውም “መስማት የተሳናቸው አዘውትረው የሚጠቀሙባቸውን ምልክቶች በመምረጥ፣ “ዓለም አቀፍ” የሆኑ ምልክቶችን እንዳሉ በመውሰድ በባሕላችን ውስጥ ጎላ ብለው የሚታዩትን መርጦ በማስገባትና ከሰሜን አሜሪካው የምልክት ቋንቋም  ጥራትና ተስማሚነት ያላቸውን እንዳሉ በመውሰድ” (ሀ መጽሃፍ፣ 1971 ) በ1968 ዓ.ም ሥራውን አጠናቆ ለትምህርት ሚኒሥቴር አስረከበ፡፡ “ከትምህርት ሚኒሥቴር ተወክለው የነበሩት የኮሚቴው ዓባላት በመጽሐፉ ይዘት ላይ ያደረጉት ምንም ዓይነት አስተዋፅዖ አልነበረም” (ተክለሃይማኖት፣ 2004)፡፡ ኮሚቴው ሥራውን እንዳጠናቀቀ የአርትዖት ሥራ ለማኅበሩ ተሠጠ፡፡ የሥዕል ሥራውም ማኅበሩ ባለሙያ ፈልጎ እንዲያሠራ ስለተባለ፣ ማኅበሩ ከዓባላቱ መካከል ሠዓሊ አቅርቧል፡፡ ለሠዓሊው የሚከፈለውን ዓበል ሁለቱ ትምህርት ቤቶች እንዲሸፍኑ ሲደረግ፣ ትምህርት ሚኒሥቴር ደግሞ የመማሪያ መጽሐፍ እንደሚያሳትመው፣ ሁሉ መዝገበ ምልክቱንም እንዲያሳትም ኮሚቴው ተስማማ፡፡

1ኛ መጽሐፍ የመጀመሪያው መዝገበ-ምልክት (1972 ዓ.ም)

     ከሦስት ዓመታት በኋላ በ1971 ዓ.ም “የአማርኛ የምልክት ቋንቋ መስማትና መናገር ለተሳናቸው፣ ሀ 1ኛ መጽሐፍ” የሚል  ርእስ የተሠጠው 15 ምዕራፎችና የአንድ ሺ ዘጠኝ ምልክቶች ሥዕልና 270 ያህል ሥዕል አልባ የምልክቶች መግለጫ የያዘ የመጀመሪያው መዝገበ-ምልክት ታትሞ ወጣ፡፡ መዝገበ ምልክቱ የሐረግና የሥዕል መግለጫዎች እንዲሁም የድርጊትና የአቅጣጫ ማመልከቻ መስመሮችና ቀስቶች የነበረው ስለ ነበር ለመረዳት ቀላል ነበር፡፡ የዝግጅቱ ዓላማም መስማት የተሳናቸውን “ለመርዳት የሚሹ ሁሉ እንደ መንደርደሪያ ሆኖ እንደሚረዳቸውና በተለይም ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መነጋገር እንዲችሉ” ታስቦ ነበር፡፡

     ይህ የመጀመሪያው መዝገበ ምልክት ለምን “የአማርኛ ምልክት ቋንቋ” እንደ ተባለ ከአዘጋጆቹ አንዱ እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡-

  •  ዋነኛው ምክንያት በወቅቱ አዘጋጆቹ ስለ ምልክት ቋንቋ የነበረን ዕውቀት ውሱን መሆኑ ነበር፡፡ በወቅቱ እንጠቀምበት የነበረው በሰሜን አሜሪካና በስውዲን አገሮች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ መስማት የተሳናቸው የሚጠቀሙባቸውን የምልክት ቋንቋዎች ሲሆኑ፣ በመጽሐፍ መልክ ሲመጡ ደግሞ ፍቻቸው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነበር፡፡ ስለዚህ ይታወቁ የነበሩት የእንግሊዠኛ ምልክት ቋንቋ ተብለው ነበር፡፡ ፍቻቸው በእንግሊዘኛ ቋንቋ በመሆኑ አብዛኞች መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች፣ የመስማት የተሳናቸው ወላጆች እና ሌሎች የምልክት ቋንቋ የመማር ፍላጎት የነበራቸው ኢትዮጵያውያን በመጽሐፉ ለመጠቀም አይችሉም ነበር፡፡ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ምልክት ለማዘጋጀት ስንነሣ ዋነኛ ዓላማችን ይህንን ችግር በመፍታት መጽሐፎቹ በሁሉም ሰው እጅ እንዲገቡና ቋንቋው እንዲስፋፋ በማድረግ ላይ ያተኮረ ነበረ፡፡ የመጽሐፉን ርእስ አማርኛ ያልነው ምልክቱ አማርኛ ነው ለማለት ሳይሆን የመዝገበ ምልክቱ መግለጫዎች እንደ ሌሎች በእንግሊዘኛ ሳይሆኑ በአማርኛ መሆናቸውን ለመጠቆም ነበር፡፡ (ተክለሃይማኖት፣ 2004)

    የዚህ መዝገበ-ምልክት ህትመት ለኢምቋ ዕውቅናና ተቀባይነት እንዲሁም መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ከመዝገበ-ምልክቱ ህትመት በኋላ ኢምቋ መስፋፋትና ማደግ ጀመረ፡፡ ይህንኑ ተከትሎም መዝገበ-ምልክቱ የያዛቸው ምልክቶች በአብዛኛው ከአሜሪካና ከስዊድን የምልክት የቋንቋዎች የተወሰዱ ስለሆኑ፣ የመዝገበ-ምልክቱ ርዕስም የኢትዮጵያ ሳይሆን የአማርኛ የምልክት ቋንቋ ስለሚል፣ የተዘጋጀውም ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከታቸው መስማት የተሳናቸው ባለመሆኑ መሻሻል አለበት የሚል አቋም በተጠቃሚዎቹ ዘንድ መንፀባረቅ ጀመረ፡፡ ሆኖም ሐሳቡ የሁሉም ድጋፍ ስላልነበረውና የመስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበርም ካለ መንግሥት ድጋፍ መዝገበ-ምልክት የማዘጋጀት አቅም ስላልነበረው እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ዕቅዱ እውን አልሆነም፡፡

     ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ምልክት የማዘጋጀት ሙከራ የተደረገው ከ18 ዓመታት በኋላ በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ በመንግሥታዊ ዐካል ነበር፡፡ በ1986 ዓ.ም. በሙያና ልዩ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ማስተባበሪያ፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ቡድን ረቂቁ ተዘጋጅቶ በትምህርት ሚኒሥቴር የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ሚያዝያ 1990 ዓ.ም የታተመው (በኮምፒውተር ተባዝቶ በእጅ ነው የተጠረዘው) ይህ መዝገበ ምልክት “የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት፣ ሁለተኛ መጽሐፍ” የሚል ርእስ ያለው ሲሆን 1314 ምልክቶች አሉት፡፡ ዝግጅቱ ከጅምሩ የቋንቋውን ባለቤቶችና ማኅበሩን ባለማካተቱ መዝገበ ምልክቱ በመስማት የተሳናቸው ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

     በ1994 ዓ.ም የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር የምልክት ቋንቋ ልማት ፕሮጀክት አዘጋጅቶ በፊንላንድ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር በኩል ለፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር አቀረበ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒሥትሩም ከ85 ሺ ዩሮ በላይ በመለገሱ የመዝገበ ምልክት ማዘጋጀቱ ሥራ በ1994 ዓ.ም ተጀምሮ ከስድስት ዓመታት በኋላ በ2000 ዓ.ም ለኅትመት በቃ፡፡ ይህ በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር በመታተም የመጀመሪያው፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግን ሁለተኛ (ሁለተኛው መዝገበ ምልክት ከተቆጠረ ሦስተኛ) የሆነው መዝገበ ምልክት በ25 ርዕሶች ዙሪያ 1322 ምልክቶች የያዙ 464 ገጾች አሉት፡፡ ይህ መዝገበ-ምልክት በይዘቱና በዓይነቱ ከመጀመሪያው ወይም ሀ መጽሐፍ በብዙ መልኩ ይለያል፡፡ አንደኛ፣ ብሔራዊ ይዘት አለው፣ ርእሱ በትምህርት ሚኒሥቴር እንደ ታተመው መዝገበ ምልክት “የአማርኛ የምልክት ቋንቋ” ሳይሆን፣ “የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ” የሚል ነው፡፡ ሁለተኛ ምልክቶቹ የቀረቡት በሥዕል ሳይሆን በፎቶግራፎች ሲሆን፣ እንደ አስፈላጊነቱ ለአንድ ምልክት ከአንድ በላይ ፎቶግራፎች አሉት፡፡ ሦስተኛ፣ ቃላቶቹ የተጻፉት በአማርኛና በእንግሊዘኛ ስለሆነ፣ አማርኛ ማንበብ የማይችሉም ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ አራተኛ፡ ከፊንላንድ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ምልክት በተውሶ የተወሰዱ የምልክቶች ክንዋኔ ማመልከቻ ቀስቶች ስላሉት የምልክቶች አሠራርን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ አምስተኛ፣ አብዛኞቹ ምልክቶቹ ሀገር በቀል ናቸው፡፡ ስድስተኛ፣ ዲዛይኑና ቅንብሩ የተሻለ ነው፡፡ ሰባተኛ፡ የሥነ ልሳን ባለሙያዎችን ያካተተ ነበር፡፡ በሁሉም መሥፈርቶች ይህ መዝገብ-ምልክት እስካሁን ከታተሙት መዝገበ-ምልክቶቹ ሁሉ የተሻለና በስፋት የተሰራጨ ነው፡፡ በመጀመሪያ አካባቢ “የደናቁርት ቋንቋ” በኋላም “የአማርኛ ምልክት ቋንቋ” በሚል መጠሪያ ይታወቅ የነበረው ቋንቋ ዛሬ የሚጠራበትን “የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ” የሚል ስያሜ ያገኘው ከዚህ መዝገበ-ምልክት ኅትመት በኋላ ነው፡፡

በኢምቋ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ካላቸው ክንውኖች ውስጥ አንዱ በ2000 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋና የመስማት የተሳናቸው ባሕል ጥናት ትምህርት ክፍል መከፈቱ ነው፡፡ ይህ የቅድመ ምረቃ መርሐግብር በዓይነቱ በአፍሪካ የመጀመሪያው እንደሆነ ይታመናል፡፡ የዚህ ትምህርት ክፍል መከፈት የኢምቋን መማር-ማስተማርና ማስተርጎምን ለማዘመን የሚረዱ ባለሙያዎችን ከማፍራት በተጨማሪ  በኢምቋ ላይ ሳይንሳዊ ጥናቶችን ለማድረግና ቋንቋውን ለመሠነድ የሚያስችሉ ምቹ አጋጣሚዎችን ፈጥሯል፡፡ በዚህ ትምህርት ክፍል ውስጥ ከመቶ በላይ የቅድመ ምረቃና ከአስር በላይ የድኅረ ምረቃ ጥናቶች የተደረጉ ሲሆን ከእነዚህ ጥናቶች ውስጥ አራቱ በዶክተሬት ደረጃ የተደረጉ ናቸው፡፡

ሁለተኛው መዝገበ-ምልክት (2000 ዓ.ም)

እነዚህ ጥናቶች የኢምቋ የቋንቋ መሥፈርቶችን የሚያሟላና የራሱ የሰዋሰው ስርዓቶች ያሉት ቋንቋ መሆኑን እንዲሁም ከአማርኛም ሆነ ከሌሎች ሀገራዊ ቋንቋዎች የተለየ ቋንቋ መሆኑን ከማረጋገጥ በተጨማሪ በሁሉም የፌድሬሽኑ ክልሎች ውስጥ ከመስማት የተሳናቸው ጋር ለመግባባትና መስማት የተሳናቸውን ለማስተማር በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በትምህርት ክፍሉ ሥር የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች የቀጠሉ ሲሆን ሁሉንም የኢምቋን የሥነ ልሳን ክፍሎች አጥንቶ የመሠነድ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢምቋ በሁሉም ክልሎች በሥፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የኢምቋ አጠቃቀም ተመሳሳይነት የጎላና ያሉት የምልክቶች ልዩነት ጠባብ በመሆኑ ሁሉም የኢምቋ ተጠቃሚዎች ያለምንም ችግር እየተግባቡበት እንደሆነ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡