መዝገበ- ምልክቱ
ይህ መዝገበ-ምልክት እስካሁን ካሉት የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ መዝገበ-ምልክቶች በተሻለ ሁኔታ ሰፊ ሆኖ የተዘጋጀ ሲሆን ለተማሪዎች፣ ለቋንቋና ባህል አፍቃሪያን ፣ ለአስተርጓሚዎች፣ በቤት ውስጥ ለሚያጠኑ፣ ለወላጆች እና ባለሙያዎች መማሪያና ማጣቀሻ እንዲሆን ምቹ ሆኖ የተዘጋጀ የመጀመሪያው ዲጅታል መዝገበ- ምልክት ነው። ይህን መዝገበ-ምልክት የተለየ የሚያደርገው ዋናው የጥናት እና የቪዲዮ ቡድን አባላት ሁሉም መስማት የተሳናቸው ከመሆናቸው ባሻገር ፤ ቡድኖቹ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው መስማት የተሳነው የስነልሳን ባለሙያ መመራታቸው ነው። የጥናት ቡድኑ በሀገሪቱ ሀያ አንድ ቦታዎች በመዘዋወር የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ከሚጠቀሙ 75 በላይ መስማት የተሳናቸው ግለሰቦች መረጃ ሰብስቧል። አብዛኛዎቹም መረጃ ሰጪዎች ከልደት ጀምሮ የምልክት ቋንቋን የሚጠቀሙ መስማት የተሳናቸው ናቸው። ምልክቶቹ ለህትመት ከመብቃታቸው በፊት በተለያዩ የማጣሪያና ማረጋገጫ ሂደቶች ውስጥ እንዲያልፉ ተደርጓል።
ለተጠቃሚዎች ማስታወሻ
የምልክት ቋንቋዎች እንደ ድምጽ ቋንቋዎች አይደሉም ከሚለው ልማዳዊ የተሳሳተ አስተሳሰብ ተቃራኒ በሆነ መልኩ የምልክት ቋንቋዎች እንደማንኛውም የድምጽ ቋንቋ የዳበሩ እና ውስብስብ ናቸው። የቋንቋ ምሁራን በብዙ የምልክት ቋንቋዎች ላይ ጥናቶችን ያካሄዱ ሲሆን በሁሉም ቋንቋዎች ውስጥ የሚገኙ መሰረታዊ ባህሪያትን በምልክት ቋንቋዎች ውስጥ ማግኘት ችለዋል። ይህ በኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ውስጥም እውነት ሆኖ ይገኛል። አንድ ሰው የአንድን ቋንቋ ቃላት ብቻ በመማር ቋንቋውን አጣርቶ ለመናገር እንደማይችል ሁሉ የአንድን የምልክት ቋንቋ ምልክቶች ብቻ በመማር ያንን የምልክት ቋንቋን መናገር አይችልም። የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ምልክቶችን መማር ፤ የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋን ከመማር ጋር አቻ ነው ማለት አይደለም። የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋን መማር ምልክቶቹን ብቻ ከመማር ያለፈ ነው። ምልክቶች ለቋንቋው ልክ እንደ አንድ ዋና ግብዓት ናቸው ብቸኛ ግን አይደሉም። ስለዚህ የሚከተሉት ነጥቦች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።
አውዳዊ ፍቺ: በመዝገበ-ምልክቱ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ምልክቶች በተለያዩ አውዶች እና/ ወይም አረፍተ-ነገሮች ውስጥ አንድ አይነት ትርጉም ላይኖራቸው ይችላል። የምልክቱ ወይም ሀረጉ ትርጉም እንደየ ዓረፍተ-ነገሩ ወይም አውዱ(ሁኔታው) ሊለያይ ይችላል።
ሰዋሰው: ብዙ የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ምልክቶች፣ በተለይ በመዝገበ-ምልክቱ ውስጥ የሚገኙ ግሶች “ግንድ” ናቸው። ብዙዎቹ በኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ምልክቶች ዐረፍተ-ነገሮች ውስጥ ጥቅም ላይ በሚውሉበት ግዜ እንደ አገባባቸው የቅርጽ ወይም የእንቅስቃሴ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ አስቀድሞ መረዳት ጠቃሚ ነው። በኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ አጠቃቀም ወቅት በምልክቱ አምስት ክፍሎች አንዱ ላይ ማለትም የእጅ ቅርጽ ፣ የእጅ እንቅስቃሴ፣ የመዳፍ አቅጣጫ፣ እጅ የሚያርፍበት ቦታ፣ እና ሌሎች በእጅ የማንሰራቸው ምልክቶች (ለምሳሌ የፊት ገለጻዎች) የሚደረግ ለውጥ ወይም ማሻሻያ የትርጉም ለውጥ ሊያስከትል ወይም የተሳሳተ መልእክት ሊያስተላልፍ እንደሚችል ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል፡፡
ልዩነቶች: አንዳንድ የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ምልክቶች አካባቢያዊ (እና የትውልድ) ልዩነቶች ሊኖራቸው ይችላል። በተቻለ መጠን የተወሰኑ የተለመዱ ልዩነቶችን ለማካተት ተሞክሯል። ቢሆንም ለየት ያሉ አካባቢያዊ ልዩነቶችን ለማወቅ በአካባቢው ካለው የመስማት የተሳናቸው ማህበረሰብ ጋር ግንኙነት ማድረግ ይኖርብዎታል።
የጣት ፊደላት: በአንድ ቋንቋ ውስጥ አንድን ሃሳብ መግለጽ የሚችል ቃል ሲጠፋ ከሌላ ቋንቋ ቃል መዋስ የተለመደ ነው። በምልክት ቋንቋ ውስጥ የጣት ፊደላት ምልክት የሌላቸው ቃላትን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ (ኢምቋ) ህይወት ያለው ቋንቋ ነው፡፡ እንደማንኛውም የንግግር ቋንቋ ቀጣይ በሆነ መልኩ እየተገነባና እያደገ ሊሄድ የሚችል ቋንቋ ነው። የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋን በትክክለኛው መንገድ ለመጠቀም ያለው የተሻለ መንገድ መስማት ከተሳናቸው የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ተጠቃሚዎች ጋር ቀን በቀን ግንኙነት ማድረግና በቋንቋው መግባባት ነው።